«ፊቼ»፣ «ጊፋታ»፣ «ያሆዴ» እና «ጋሪ ዎሮ» – የብሔረሰቦቻችን ዘመን መለወጫዎች

በአብረሃም ተወልደ

የኢትዮጵያ ሕዝብ በየዓመቱ በታላቅ ስሜት ከሚያከብራቸው በዓላት ውስጥ የዘመን መለወጫ በዓሎቻቸው በዋናነት ይነሳሉ። በእነዚህ በዓላት ሰው እንደ ዕፅዋት ሁሉ መስከረምን ይዞ በተስፋ ስሜት ይለመልማል። በአልባሳት፣ ያጌጣል፤ የሚመገበውንም አዘጋጅቶ በአብሮነት ይመገባል። ከሚያበሩት ችቦና ከሚያነዱት እሳት ባሻገር በግርማ ምሽት እንዲገኑም የሚያደርግ ልዩ ጊዜያቸው ነው። ይህ ዘመን መለወጫ በአገሪቱ የተወሰኑ ቦታዎች በብዛት የሚታይ ቢሆንም ሁሉም መሰረታቸው ዘመንን መተካታቸውና ለብርሃን መብቃታቸው ነው። እናም እኛም የዘመን መለወጫ ስያሜ ሰጥተው ከሚያከብሩት ዞኖች መካከል የተወሰኑትን ልናካፍላችሁ ወደናልና እንካችሁ።

”ጋሪ ዎሮ”

”ጋሪ ዎሮ” ወይም “ጋሮ” እየተባለ ከሚጠራው እንጀምር። በቦሮ-ሺናሻ ብሔረሰብ የሚከበር ሲሆን፤ የሚከበረውም መስከረም 17 ምድሩ በአደይ አበባ አሸብርቆና ክረምቱ አልቆ ፀደይ ወቅት ሲገባ ነው። ምሳሌነቱም ብርሃን መጣ ለማለት ነው። እናም በዚህ እለት ማለትም በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ በየቤቱ በብሔረሰቡ አባቶች ተመርቆ ያከብሩታል። በብሔረሰቡ ቋንቋ “ጋ ሪጀባ” በሚባል ቦታ ላይም ነው ደመራው የሚለኮሰው።

በበዓሉ ይዘት ያተኮሩ ሶስት ዓይነት ዘፈኖች ይዘፈናሉ። የዘፈን ወቅቶችም አሉት። እነዚህም ከሐምሌ ወር መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ እስከ በዓሉ ዋዜማ አካባቢ፣ ከበዓሉ ዋዜማ አካባቢ ጀምሮ እስከ በዓሉ ዕለት እና ከበዓሉ በኋላ እስከ ሁለት ሳምንት ድረስ የሚሉት ናቸው። በሺናሻዎች ዘንድ ዘመን መለወጫ አዲስ እሸት፤ ለምግብነት የደረሱ የእህል ዓይነቶች በሙሉ በዚሁ በአንድነት በሚከበረው ቦታ ቀርበው በአባቶች ተመርቆ ለምግብ ይውላል።

በዘመን መለወጫው ብዙ ጊዜ የወጣቶቹ ጭፈራ የሚያጠነጥነው አዲስ ዘመን መጣልን፣ ጨለማን ጥለን አለፍን” በሚሉትና አዲስ ዓመት ደረሰልን፣ ችግራችን ተወገደ፣ አይናችን በራ፣ አዲስ ዘመን ተቀበልን በማለት ነው። ሌላው የበዓሉ አከባበር አካል የሆነው ደግሞ የብሔረሰቡ አባላት በየቤታቸው እንደየአቅማቸው አስፈላጊውን የምግብና መጠጥ ዝግጅት በማድረግ በዓሉን በደማቅ ሁኔታ ማክበራቸው ነው።

የ“ጋሮ” ስነ-ስርዓት ከመፈፀሙ በፊት መስከረም 16 ምሽት ለደመራ የሚሆን ከ4 እስከ 12 እርጥብ እንጨት ጐረምሶች “እንኳን ለአዲስ ዓመት አደረሰን” በማለት በየቤታቸው ያስገባሉ። ይህም በብሔረሰቡ ቋንቋ “ጋርጊንድጌዳ” ይባላል። ከዚያ ያ የመጣው እንጨት ተሰብስቦ በሚከበረው ቦታ ላይ ይደመራል፤ ሁሉም ሰው ከተሰበሰበ በኋላም በታዋቂ ሽማግሌዎች ምረቃም ይተከላል። በዚህ በዘመን መለወጫ ዕለት በየቤቱ ቤተዘመዶች ከታላቃቸው ቤት በመጀመር “የአባቴ አምላክ ከባለፈው ዓመት ለዘንድሮ አድርሶናልና ለዘንድሮ ያደረሰን ደግሞ ለአዲሱ ዓመት እንኳን በሰላም አደረሰን” በማለት የሙታን አያታቸውን እና አባታቸውን አምላክ በመጥራት በቤቱ ውስጥ የመለማመኛና የምርቃት ስርዓት ያዘጋጃሉ። በባህሉ መሰረት የተዘጋጀውን ‹‹ጭምቦ›› በትንሹ በመቁረስ ወደ መሬት በመጣልና ‹‹ቦርዴውን››ም በትንሹ መሬት ላይ በመድፋት ይለማመናሉ። ይህም በብሔረሱ ቋንቋ “ሚሽቂራ” ይባላል። ከዚያ በመቀጠል የሚያደርጉት ሁሉም ቤተሰብ ተሰባስቦ በአንድ መሶብ ዙሪያ ከቦ ጭምቦውን መመገብ ነው።

በጋሮ ጊዜ የተጣላ የቤተሰብ አባል ካለ ተፈልጎ እርቅ ይፈጽማል፤ በዓሉንም አብሮ ያከብራል። ጥፋተኛ ተለይቶ ተበዳዩን እንዲክስና ተበዳዩም ይቅር እንዲልም ይደረጋል። በነጋታው ደግሞ ዘመድ አዝማድ ጋር ይጠያየቃል። ቤት ሲገባም እንደየአካባቢው “ወርገወ” ወይም “ዎሮ ዎሮ” ሲል መላሽ/ባለቤቶች ደግሞ “ዎሮ ቦሬ” ይላሉ። ትርጉሙም “አንቁጣጣሽ-እንኳን ደህና መጣሽ” እንደ ማለት ነው።

ደመራው የተለኮሰበት ቦታ እስከ መስከረም 18 ድረስ የሚጨፈርበት ይህ የዘመን መለወጫ፤ በመስከረም 18 ማታ ወደ አስር ሰዓት ገደማ የሀገር ሽማግሌዎቹ በመሰብሰብ “ለአዲሱ ዓመት ያደረሰን አምላክ ለመጪው ዓመትም በሰላም ያድርሰን፤ ዓመቱ የሠላም፤ የደስታና የፍሰሀ ዘመን ይሁንልን፤ ምርቱ ረድዔትና በረከት ይኑረው፤ ሀብትና ንብረት ይለምልም ወዘተ” በማለት መርቀው ህዝቡን ያሰናብታሉ።

«ፊቼ ጫምባላላ»

‹‹ፊቼ ጫምባላላ›› በመባል የሚታወቀው የሲዳማዎች የዘመን መለወጫ በዓል በከዋክብት ዑደት ላይ የተመሠረተ ቀመር አለው። ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ በመሆኑም በምሕፃሩ ዩኔስኮ የሚባለው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት በቅርስነት መዝግቦታል።

የሲዳማ ዞን ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገነነ አበራ እንደሚናገሩት፤ የፊቼ በዓል አፈ ታሪኩ ሲታይ መጠሪያውን ፊቾ ከምትባል የሲዳማ ሴት የተገኘ ነው። ፊቾ ዕድሜዋ ለአቅመ ሔዋን ሲደርስ በሲዳማ ብሔር ባህልና ሥርዓት መሠረት ተዳረች። ከዚያ ይህች ሴት በየዓመቱ ለወላጆቿ፣ ወንድሞቿ፣ ለዘመድ አዝማድና ጎረቤት ቡርሰሜ (ከእንሰት ላይ የሚፋቅ ቆጮ በእሳት ላይ ተነኩሮ እና ቅቤ በብዛት ተጨምሮበት የሚዘጋጅ ባሕላዊ ምግብ) እና እርጎ በመያዝ የዓመቱ በሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል በሚውልበት ዕለት በቋሚነት ትጠይቃቸው ነበር።

በዓሉ የሚውለው በተመሳሳይ ቃዋዶ (በሲዳማ ብሔር የቀን አቆጣጠር የሳምንቱ የመጀመርያ ቀን) ላይ ሲሆን፤ በአፈታሪኩ መሠረት ፊቾ ያመጣችውንም ምግብ በዚሁ ዕለት ምሽት ላይ ዘመድ አዝማድ፣ የአካባቢ ጎረቤትና ቤተሰብ ተሰባስበው ይመገቡት ነበርና ያ መነሻ ተደርጎ እንደሚከበር ያስረዳሉ። አባቷና ታዳሚዎች ዘወትር የፊቾን ደግነትና ያመጣችውን ምግብ በማድነቅ ይመርቋታል። ፊቾ ይህንን በተደጋጋሚ ስትፈጽም ቆይታ ከዚህ ዓለም በሞት ስትለይ የአካባቢው ነዋሪዎች ፊቾ በመሞቷ ጥልቅ ሐዘን የተሰማቸው ከመሆኑም በላይ የሷ ድግስ ታዳሚ የነበሩ ሰዎች ይህችን ሩህሩህ ደስታ ፈጣሪ ሴት በዘላቂነት ለማስታወስ ቀደም ሲል እርሷ ምግብ ይዛ የምትመጣበትንና ግብዣው የሚካሄድበትን የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ ቀን በስሟ ፊቼ ብለው እንደሰየሙትም ይናገራሉ። የፊቼ በዓል ሁሌም በቃዋዶ ቀን የሚውልበት ምክንያት ደግሞ ቀኑ በብሔሩ የሳምንቱ የመጀመርያውና ታላቅ ቀን ተደርጎ ስለሚቆጠር እንደሆነ የሚያነሱት አቶ ገነነ፤ በዓሉ ሁሉም ሰውና ከብቶች የሚያርፈበት፤ የተጣላ ፍቼ ጨምበላላ ማለትም አዲስ ዓመት ሳይገባ ይቅርታ የሚጠይቅበት ነው። የተፋቱ ባል እና ሚስት ቢኖሩ እንኳን በዋዜማው ቀን ተጣልታ የወጣችበት ቤት ማለት የቀድሞ ባሏ ጋር ሄዳ እርቅ ማድረግ ይኖርባታል። ምክንያቱም በዓሉ የእርቅ ዘመን ነውና ይላሉ።

የፊቼ ጫምባላላ በዓልን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥናቱን የሠሩት ባለሙያው አቶ ገዛኸኝ ግርማ እንደገለጹት፣ በዓሉ በቤተሰብና በጎረቤት ደረጃ ተሰባስቦ በማክበር የሚጀምርና ከዚያም እየሰፋ በመሄድ በባህላዊ አደባባይ (ጉዱማሌ) በጋራ የማክበር ሒደትን ያጠቃልላል። ፊቼ ከዘመን መለወጫ በዓልነት ፋይዳው ባሻገር ባህላዊና ማኀበራዊ ፋይዳዎች ያሉት፤ ሀገር በቀል የሆነ የዘመን አቆጣጠር ዕውቀትን ያካተተ፤ የሲዳማ ብሔር አንኳር የሆኑ ባህላዊ ገጽታዎች የሚንፀባረቁበት ግዙፍነት የሌለው ወይም የማይዳሰስ ቅርስ ነው።

የፊቼ በዓል ሰላም፣ መከባባር፣ መቻቻል እንዲሰፍን፣ ዕርቅ እንዲወርድ እንዲሁም ልማት እንዲፋጠንና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ የጎሳ መሪዎች እና የበቁ አረጋውያን ለኅብረተሰቡ በሰፊው ትምህርት የሚሰጡበትም ወቅት ነው። እናም በዚህ ጊዜ አቶ ገነነ እንደሚሉት፤ በመጀመርያ ላኦ (ምልከታ) ይካሄዳል። ማለትም በዓሉ የሚውልበት ቀን በየዓመቱ ተመሳሳይ ስለማይሆን በባህላዊ ቀን ቆጠራ ስሌትና የሥነ ክዋክብት ምልከታ ቀኑ ይለያል። ይህንን ተግባር የሚፈጽሙት ‹‹አያንቶ›› የተሰኙ የሥነ ክዋክብት ጠበብቶች ሲሆኑ፤ ቡሳ የተሰኙ ኅብረ ክዋክብት ከጨረቃ አቀማመጥ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማገናዘብ ማለትም የክዋክብቱ ከጨረቃ የመቅደምና ወደ ኋላ የመቅረት ሁኔታ በትኩረት በመከታተል በተለይ ከክዋክብቱ መካከል አውራ የሆነችው ኮከብ ከጨረቃ መቅደሟን ሲያረጋግጡ ፊቼ በቀጣይ ቀናት ውስጥ ባለው የቃዋዶ ዕለት እንደሚውል ይናገራሉ። የሚነግሩትም ለጎሳ መሪዎች (ገሮ) ነው። አያንቶዎች ባቀረቡት ሐሳብ ላይ ተመሥርተው የጎሳ መሪዎች ከጪሜሳዎች (የበቁ አረጋውያን) ጋር ሶንጎ (የአዛውንቶች ስብሰባ) በማድረግ በጉዳዩ ላይ ከተወያዩ በኋላ ቀኑ በአዋጅ ለኅብረተሰቡ እንዲገለጽ ስምምነት ይደርሳሉ። የጎሳ መሪዎችም በየአካባቢያቸው በሚገኙ የገበያ ሥፍራዎች የበግ ቆዳ ረዥም ዘንግ ላይ ሰቅለው በመያዝ ለኅብረተሰቡ የፊቼ በዓል የሚውልበትን ቀን ያውጃሉ (ላላዋ ያደርጋሉ)። ከዚያ በኋላ ‹‹ሳፎቴ ቄጣላ›› (የመጀመርያው ባህላዊ ጭፈራ) እንደሚካሄድም ያብራራሉ።

ያሆዴ መስቀላ

ያሆዴ በሀዲያ ብሔር የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ ነው። አዲሱ ዓመት የሰላም የፍቅር፣ የብልፅግና እንዲሆን የሚመኙበት በዓል በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ይከበራል። በዓሉ የብርሃን የአዲስ ሕይወት ማብሰሪያ ያለፈው አሮጌ ዓመት የሚረሳበት፣ የተጣላ የሚታረቅበት፣ በተለያየ ምክንያት ከአካባቢው እርቀው የሚኖሩ ከወላጆቻቸው ጋር የሚገናኙበት ታላቅ ክብረ በዓል ነው። ለትዳር የደረሱ ወጣቶችም ቢሆኑ የሚተጫጩበት ነው።

የሀዲያ ዞን ምክር ቤት አማካሪ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሳሙኤል ዘመድኩን ያሆዴ መስቀላን እንደሚከተለው አብራርተውታል፤ ያሆዴ መስቀላ ለሀዲያ ሕዝብ ብዙ ነገሩ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ያሆዴ ለሀዲያ ህዝብ የሁሉም ነገር መጀመሪያው ነው። በዚህም የተነሳ መስቀል ሲመጣ ያሆዴ መስቀላ በማለት ሁሉንም ነገር አንድ ብሎ ይጀምራል። አዲስ ዓመቱንም ይቀበላል። ማንኛውንም ክስተት የሚዘግበውና የሚያስታውሰው በዛ ዓመት ነው።

በያሆዴ መስቀላ ዕለት ማታ ፉኒታ ( ሆያ ሆዬ) ጨፋሪዎች ደግሞ ከዚህ ቤት ችጋር ውጣ፤ በሽታ ውጣ የሚሉበትና የሚጨፍሩበት ነው። ጨፋሪዎች መርቀው ሲወጡ የቤቱ አባውራና እማወራ ደግሞ እናንተም እደጉ በማለት ይመርቁበታል። በዚህ በዓል ሴቶችም ከአለባበስ እስከ ፀጉር አሰራር ድረስ በተስተካከለ ሁኔታ ይዘጋጃሉ። የሀገር ሽማግሌዎች በሰልፍ ሆነው ስርዓቱን ያስጀምራሉ፤ ይከታተላሉ፤ ይመርቃሉም።

በዚህ በዓል ሴቶች ቀደም ብለው ስራቸውን ይጀምራሉ። ቤታቸውን ያዘጋጃሉ። በህብረት ስራ ይሰራሉ። ወንዶች ደግሞ እንጨት ያዘጋጃሉ። ሰንጋ ይገዛሉ። ህፃናት ጦምቦራ (ችቦ) ቀድመው ይሰራሉ። የዘመን መለወጫው ሲደርስ ደግሞ ሰው ብቻ ሳይሆን ከብቶችም አዲስ ዓመት የሚቀይሩበት በመሆኑ ከአምስት ወር ጀምሮ ጥብቅ ወይም ክልክል ሳር ይዘጋጅላቸዋል።

በሀዲያ አዲስ ዓመትን ለመቀበል በቅድሚያ አንድ ሰው ከተጣላው ሰው ጋር እርቅ ሰላም ማውረድ አለበት። ቂም ይዞ አዲሱን ዓመት መቀበልም ሆነ ማንኛውንም አይነት ዝግጅት ማድረግ አይችልም። ከዚያ በኋላ ነው ለበዓሉ ዝግጅት የሚጀምሩት። በሀድያዎች ዘንድ ከአስራ አምስት ቀናት አስቀድሞ የሚጀመረው ‹‹የመቻዕል ሜራ›› የበዓል ዝግጅት የሚደረግበት ገበያ የእብድ ገበያ ይባላል። መቻዕል ሜራ የሚለውን ቃል የያዘውን ፅንሰ ሀሳብ በአቻ ለመግለጽ አስቸጋሪ ቢሆንም ሀሳቡ የእብድ ገበያ እንደማለትም ነው። እናም በብሔሩ ባህላዊ እንድምታ ያለውና የገበያ ተጓዦች ስርዓት ሲሆን ከትውልድ ቀያቸው እርቀው የሚኖሩትን የማህበረሰብ አካላት ሳይቀር ያገናኛል።

በዚህ ገበያ ፈጣሪ ይመሰገናል፤ ሁሉም ሰው ገበያውን ይጎበኛል፤ የማይሸጥ የማይለወጥበት ነገርም የለም። የለም የሚባል ቃል አይሰማም። ስያሜውም የእብድ ገበያ እንደመሆኑ ከሌሎች የገበያ ቀናት የሚለየው የራሱ የሆኑ በርካታ መገለጫዎችና ክንዋኔዎች ስላሉት ነው። በዚህ ወቅት ጊዜ ውድ ነው። ከጠዋቱ አስራ ሁለት ሰዓት ገበያው ስለሚደራ ወጥቶ መግዛት ያስፈልጋል። ምክንያቱም እንደመደበኛው የገበያ ቀን እስከ ማታ አይቆይም።

በሀድያዎች የዘመን መለወጫ እለት የሚበላው ‹‹አተካና›› የሚባል ባህላዊ ምግብ ሲሆን፤ አተካኒሞ ሊባልም ይችላል ያሆዴ አንድ ተብሎ መከበር ከመጀመሩ በፊት አዛውንት ችቦ ካቀጣጠሉ በኋላ የሚመገቡት ነው። በጣዕሙ ወደር አይገኝለትም። በብዛት የሚዘጋጀው ለያሆዴ መስቀላም ነው። ስለዚህ አተካና የዘመን መለወጫ ቀንን አመላካች ነው። በበዓሉ እለት ለሚመጣ እንግዳና ማታ ለጭፈራ ለሚመጡ ህፃናት ይሰጣልም። በአቅም ምክንያት አተካናን ማዘጋጀት የማትችል ሴት ካለች እንኳን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአተካና መስሪያ የሚያስፈልጉ ነገሮችን በማጠራቀም ይሰጧታል። በአሉም የሁሉም ሰው ደስታ ሆኖ ያልፋል።

ዮዮ ጊፋታ

ጊፋታ/ ግፋታ/ ማለት ትርጉሙ በኩር ወይም ታላቅ ማለት ሲሆን፣ የወላይታ ብሔረሰብ አዲስ ዓመትን አንድ ብሎ የሚጀምርበት የአዲስ ዓመት መግቢያ ብቻም ሳይሆን የብርሃን ጊዜ ማብሰሪያ ነው። የወላይታ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ እትም ላይ እንደሰፈረው፣ ጊፋታ ማለት ባይራ (ታላቅ)፣ መጀመሪያ እንደ ማለት ሲሆን፤ በሌላ በኩል ጊፋታ ማለት መሻገር ማለት ነው። ይህም ከአሮጌ ወደ አዲስ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሻገር የሚለውን ይገልጻል። ጊፋታ የዓመቱ የመጀመሪያ ወር ስያሜ ነው።

አቶ መሐመድ ሀምቢሶ ‹‹ውበት›› በተሰኘው የደቡብ ባህልና ቱሪዝም ድርሳን ላይ እንደጻፉት፣ ጊፋታ ነጭ ልብስ ተለብሶ በጋዜ (በኩር ጨዋታ) በጋራ ሆኖ በመጫወት የሚከበር ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ ነው።

ጊፋታ በወላይታዎች ዘንድ ልዩ መሆኑን የምንረዳው የበኩር ልጅ ሳይቀር የሚሰየምበት መሆኑ ነው። ማለትም ወንድ ከሆነ ‹‹ግፋቶ›› ሴት ከሆነች‹ ‹‹ግፋቴ›› ተብላ እንድትጠራ ይሆናል። መስከረም ወር በገባ ከ14 እሰከ 20 መካከል በሚውለው እሑድ ዕለት አዲሱን ዓመት የሚከበረው ይህ የወላይታዎች ዘመን መለወጫ፤ ወር በገባ አሁድ ቀን ላይ የሚከበር ሲሆን፤ በዓሉ የሚውልበት እሑድ ስምም ‹‹ሹሃ ወጋ›› የእርድ እሑድ እየተባለ ይጠራል።

በዓሉ ቃየ አሹዋ (ቃንጡዋ) ከበሬው ሥጋ ላይ ምርጥ የሆነው ክፍል ተመርጦ ቁርጥ ይሆንና በቅቤ በተለወሰ ዳጣ የሚበላ ነው። ይህ የሚሆነውም ቤተሰብ በአንድ ቦታ ተሰብስቦ ‹‹ኤርጊያ›› የሚባል የእንሰት ቅጠል በማንጠፍ ቁርጡን በመዘርገፍና ዙሪያውን ከበው በመቀመጥ በዳጣ በርበሬ እያጠቀሱና እርስ በእርስ እየተጎራረሱ በመመገብ ነው።

እንደ አቶ መሐመድ አገላለጽ፣ በወላይታ የበሬ ድለባ ሥርዓት በጣም የተለየ ሆኖ በሬ በሰው ትንፋሽ እየተጋራ ‹‹ጢሁዋ ሆምቢያ›› በሚባለው በተከደነ አጥር ውስጥ የተለያዩ የእህል ዝርያዎችን እየተመገበ ስለሚቀለብ ቁርጥ ሥጋው የተለየ ጣዕም አለው። በዚህ ምክንያት ወላይታ በጥሬ ሥጋ ቱሪዝም ትታወቃለች።

ለጥብስ የሚሆነውን ሥጋ (ጥጣ) ዘልዝለው አግድም በተዘረጋው ትልቅ እንጨት በማንጠልጠልና እሳት በማንደድ እየተጠበሰ፤ እሳት እየነደደበት የበሰለውን ሥጋ ከእሳት አውጥተው የሚመገቡት ወላይታዎች፤ የበዓል ዝግጅታቸውን የሚጀምሩት በወርኃ ሐምሌ በሚደረገው የጉልያ ስርዓት ነው።

ለጊፋታ በዓል መቀበያ ከሚዘጋጁት ምግቦች አንዱ ‹‹ጉርዱዋ›› የተባለው ምግብ ሲሆን፤ በበልግ ጊዜ ከተዘራው ገብስ የሚዘጋጅ ነው። ወንዶች ገብሱን በማጨድና በመሸክሸክ ለሚስቶቻቸው ያቀርባሉ። ከዚያም ስራው የሴቲቱ ይሆናል። ወንዶች በጊዜው ለአስራ አምስት ቀን የሚሆን የማገዶ እንጨት በጊዜ ፈልጠው ያከማቻሉ፤ ለከብቶችም የሚበቃ ሣር በበቂ ደረጃ ከነማባያው ቦሌ (አዱዋ) ያቀርባሉ። ለተለያዩ ቅመማ ቅመሞች ግዥ ለሚስቶቻቸው በቂ ገንዘብም ይሰጣሉ። ለበዓሉ ዝግጅት የሚያስፈልገውን ሥጋ ወደ ቤት ለማምጣትም ይዘጋጃሉ። ሴቶች ደግሞ ለቆጮ የሚሆን እንሰትን በጊዜ በማፋቅ ቡልአ (ቡላ) ያወጣሉ፤ ሙቿ የተባለው የቡልአ ፍርፍር እንዲዘጋጅ ያደርጋሉ። ከቆጮው ባጭራ የተባለው የሆድ ማፍታቻ ምግብ ለበዓሉ ዋዜማ ያዘጋጃሉ። ለማባያም የወላይታ ዳጣና በርበሬም እንዲሁ። የተለያዩ መጠጦች ቦርዴ፣ ጠጅ፣ ጠላ እና ወተት በትልቅ ጋንና እንስራም የማዘጋጀቱ ድርሻ የእነርሱ ነው። የቅቤ ዕቁብንም በመጣል ሴቶች ብዙ ቅቤ ያጠራቅማሉ።

ለልጆች ስጦታ መስጫ ሎሚ ገዝተው በእንስራ ያጠራቅማሉ። ለቂጣ የሚሆን የቦቆሎና የማሽላ ዱቄትም ያዘጋጃሉ።

የግፋታ በዓል ከመግባቱ በፊት ያሉት የሦስት ሳምንታት ሃሬ ሃይቆ፣ ቦቦዳ እና ጎሻ ተብለው የሚጠሩ ሲሆን፤ ሃሬ ሃይቆ የሚባለው የጳጉሜን ወር ነው። አህያ ለሽያጭም ሆነ ለበዓል ዝግጅት የሚሆን ዕቃ ከቤት ወደ ገበያ ጭና የምትወስድበት ሳምንትም ነው። ከገበያ መልስም ለቤቱ የሚያስፈልገውን ዕቃ ጭና ትመጣለች። ይህ በቀን ሁለቴ የሚጫንበት ዕረፍት የማይሰጥ አህያ ፈጅ ሳምንት ይባላልም።

ከመስከረም 1 እስከ 7 ያለው ሳምንት ደግሞ ቦቦዳ የሚባለው ሲሆን፤ ሆደ ሞርሙር እንደማለት ነው። ቤተሰብ በዓሉን ለማዘጋጀትና በደስታ ለማሳለፍ በእጃችን ምን አለ?፣ ምን ጎደለብን? በማለት በሥጋት የሚያሳልፉበት ሳምንት ነው።ሦስተኛሳምንት ደግሞ ጎሻ የሚባል ሲሆን፤ ትርጓሜውም ‹‹የዕብደት ሳምንት›› እንደማለት ነው። ሳምንቱ የዕብደት ሳምንት ተብሎ የሚጠራበት ዋናው ምክንያቱም ለበዓሉ የጎደለውን ነገር በፍጥነት ለማሟላት ምርጫ የማይሰጥ ሳምንት በመሆኑ ነው። እሑድ የአዲስ ቀን ብሥራትም ነው። የአዲሱ ዓመት 2ኛ ቀን ‹‹ታማ ሰኞ›› ይባላል። የእሳት ሰኞ ነው ትርጉሙ። በዚህ ቀን አንዱ ከአንዱ ቤት እሳት መዋዋስና መቀባበል አይቻልም። በዓመት አንድ ቀን ወላይታዎች በራሳቸው ቤት እሳት እያነደዱ የሚውሉበት ቀን ነው። የአዲስ ዓመት 4ኛ ቀን ረቡዕ ደግሞ ‹‹ጋዜ ኦሩዋ›› ይባላል። የሰፈሩ ወጣቶች በየመንደሩ በታዋቂ የአገር ሽማግሌዎች ደጅ ተሰባስበው የግፋታ በዓል ባህላዊ ጨዋታ የሆነውን ‹‹ጋዜ›› በጋራ ሆነው ‹‹ሀያያ ሌኬ ›› እያሉ ትከሻ ለትከሻ ተቃቅፈው የሚጫወቱበትና ልጃገረዶችን ሎሚ በመለመን የሚፈልጓትን የሚመርጡበት የጨዋታ ቀን ነው።

ልጃገረዶች በየቡድን ቁጭ ብለው ወንዴና ሴቴን ከበሮ እየመቱ ‹‹ወላወላሎሜ›› እያሉ ለፈለጉት ወንድ ሎሚ የሚመርጡበት፤ ወንዶች ለሚዜነትና ለጓደኝነት ከመረጧት ሴት ጋር በጥርስ አንድ ሎሚን ለሁለት የሚከፋፈሉበትና ስማቸውን ሲጠራሩ ‹‹ሎሜ ሎሜ›› የሚባባሉበትም የጨዋታ ጊዜ ነው። ስያሜውም ‹‹ጋዜ አሩዋ›› ይባላል። በወላይታዎች ባህል ጊፋታ የሚሸኘው ጥቅምት በገባ በመጀመሪያው ሳምንት ማክሰኞ ሆኖ የሽኝት በሬ ታርዶ ከተበላ በኋላ ነው። ‹‹ቶክ ጤላ›› የተባለውን ምሽት በችቦ ያባርራሉም። ዜማ በተቀላቀለበት ጩኸት ችቦ ይዘው ‹‹ኦሎ ጎሮ ባ! ሳሮ ባዳ ሳሮ ያ!›› እያሉ ጊፋታ በሰላም ሄደሽ በሰላም ነይ ይላሉ። የኢትዮጵያ አብዘሃት ውጤት የሆኑት እነዚህ በዓላት ፍቅናንና አንድነትን ለማስፈን ትልቅ ትርጉም አላቸው። እኛም እንዲህ ያሉ አገር በቀል ዕውቀቶችን እና ባህሎችን ለአገራዊ እድገት እና ለሰላም እንጠቀምበት በማለት መልካም ዘመን እንዲሆን ተመኘን!

አዲስ ዘመን መስከረም 25/2012