ኢሬቻ

በበርካታ የኦሮሞ ሕዝብ የሚከበረው ኢሬቻ (ኤሬሳ) መስከረም 23 ቀን 2013 ዓ.ም. በሆራ ፊንፊኔ፣ እንዲሁም መስከረም 24 በሆራ አርሰዲ በቢሾፍቱ ይከበራል፡፡ ከአንድ ወቅት ወደ ሌላ ወቅት መሻገሪያ ተደርጎ የሚከበረው በዓሉ ክረምት አልፎ ወደ በጋ ሲሻገር ምሥጋናና ምልጃ የሚቀርብበት በዓል ነው፡፡ በሥርዓቱም መሠረት ቃል ኪዳን ይገባል፡፡ የተገባው ይታደሳል፡፡ ካለፈው የበለጠ አንድነት ተፈጥሮ ከዘመን ወደ ዘመን ይሻገር ዘንድ ምሥጋናና ምልጃ ይከናወናል፡፡

ሁሉም ነገር የተፈጥሮ ሥርዓቱን ጠብቆ እንደሚመጣ ለመግለጽ ከፊት ለፊት ልጃገረዶች ቀጥሎ ሴቶች ‹‹ማሬዎ ማሬዎ›› እያሉና ባህላዊ ጭፈራዎችን እያሰሙ ሲጓዙ፣ አባ ገዳዎች፣ አዛውንቶች እንዲሁም ወጣቶች (ፎሌዎችና ቄሮዎች) ይከተላሉ፡፡

‹‹ኢሬቻ ሰላም ነው፣ ሰላም ጥልቅ ትርጉም አለው፣ ሰው ከሰው ጋር፣ ሰው ከራሱ ጋር፣ ሰው ከተፈጥሮ ጋርና ሰው ከፈጣሪው ጋር ሰላም ሊኖረው ይገባል፤›› የሚለው ጽንሰ ሐሳብ የክብረ በዓሉ ጭብጥ ነው፡፡

አባ ገዳዎችና አባ መልካዎች ወንዙ ዳር ሆነው ታላቅና ታናሹን እንደ ቅደም ተከተላቸው ይመርቃሉ፡፡ መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡

የኢሬቻ አከባበር

በዓሉ የራሱ የአከባበር ሥርዓትና ክንውኖች አሉት፡፡ በዋዜማው የሙዳ ሥርዓት (Sirna Muudaa) ይከናወናል፡፡ በአባ ገዳዎችና በአባ መልካዎች የሚከናወኑ የምሥጋና መስዋዕቶች፣ ጸሎት፣ ምርቃትና ዕርቅ በሐይቁ ውኃ መጠመቅ የሥነ ሥርዓቱ አካል ናቸው፡፡

በበዓሉ አከባበር ላይ በወጣት ሴቶችና ወንዶች፣ እንዲሁም በሕፃናት ጭፈራዎች፣ በአዛውንቶችና በአባ ገዳዎች አማካይነት የጋብቻ ሥነ ሥርዓቶች ይከናወናሉ፡፡ የተለያዩ የኦሮሞ ጎሳዎች በየራሳቸው ባህላዊ ጭፈራ አለባበስ በመገኘት ያከብራሉ፡፡ ባህላዊ ምግቦችም  ለበዓሉ ውበትና ድምቀት ይሰጣሉ፡፡ የኦሮሞ ኅብረ ባህል የኦሮሞ ብዝኃነትና አንድነት በአንድ ቦታ የሚታይበት ልዩ በዓልም ነው፡፡

የኢሬቻ አከባበርን በተመለከተ ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ ስንታየሁ ቶላ፣ ኢሬቻ በሕዝብ (በአገር ደረጃ በጎሳ) እንዲሁም ቤተሰብ ደረጃ ሊከበር እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡

‹‹ክብረ በዓሉ የጎሳ ወይም የመተሳሰብ ኢሬቻ በቀዬ በመኖሪያ አካባቢ ይከበራል፡፡ በጎሳ ደረጃ ሲከበር የገዳ የክብር ዕቃዎች አይወጡም›› በማለት ስለበዓሉ ያብራራሉ፡፡

የኢሬቻ በዓል በዓመት ሁለት ጊዜ ይከበራል፡፡ አንደኛው ኢሬቻ ቢራ ወይም ኢሬቻ መልካ ሲሰኝ፣ ይኼም የክረምት ወቅት አልፎ መፀው ሲገባ የሚከበር ሲሆን፣ በአብዛኛው ከመስከረም እስከ ኅዳር ድረስ ይከበራል፡፡ በመስከረም አጋማሽ ላይ ከሚከበረው ከመስቀል በዓል ማለትም አይኖ ወይም ጉባ ኮርማ በኋላ እሑድ ቀን ላይ ይከበራል፡፡ ኦሮሞ ከጥንት ጀምሮ የሚያከብረው መስቀል ‹‹እፋኖ›› ወይም ‹‹ጉባ ኦርማ›› በመባል ይታወቃል፡፡

ሌላኛው የኢሬቻ ክብረ በዓል ኢሬቻ ቢራ (መልካ) በሐይቆች ወይም በወንዞች ዳር የሚከበር ነው፡፡ አደይ አበባ፣ ለምለም ሳርና ዘንባባ ተይዞ የሚከበር ሲሆን የመፀው ወቅት መለያው ነው፡፡ ይኼም ከከባዱ የክረምት ወራት በሰላም ያሻገራቸውን ዘመድ አዝማድ መገናኘት በመቻላቸው፣ ክረምት የዘሩት የእህል ቡቃያ በማየታቸው ፈጣሪያቸውን ‹‹ዋቃ››ን ያመሠግናሉ፡፡ ከዚያም መጪው የበጋ ወራት የሰላምና የጤና እንዲሆንላቸውና የበቀለው ቡቃያ ፍሬ እንዲያፈራ ይለምናሉ፡፡ የሁለቱም በዓላት የአከባበር ሥርዓትና ልማድ ተመሳሳይ ሲሆን የሚከበርበት ወቅት ግን ይለያያል፡፡

‹‹ዋቄፈና›› የኦሮሞ ሕዝብ ሃይማኖት

የኦሮሞ ሕዝብ ሃይማኖት ዋቄፈና በመባል ይታወቃል፡፡ ዋቄፈና በአንድ ዋቃ (አምላክ) ማመን ነው፡፡ ይህ አምላክ ጥቁር ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ዋቃ ጉራቻ በመባልም ይጠራል፡፡ ጥቁርነቱ ከኃያሎች ሁሉ ኃያል፣ ንፅህነቱና የአምላክነቱ መገለጫ እንደሆነ ይታመናል፡፡

በዚህም መሠረት ዋቃ ሁሉም ቦታ ያለ፣ ሁሉም በእሱ የሆነ፣ ሁሉን የፈጠረና ሁሉን ማድረግ የሚችል እንደሆነ የጥንታዊ ኩሾች ባህል፣ ፍልስፍና ዕውቀትና ሥልጣኔ የዋቄፈና እምነት መሠረቶች እንደሆኑ ስለዘርፉ ያጠኑ ያስተምራሉ፡፡ በተለያዩ ጥናቶች መሠረትም ኢሬቻ በወንዞች ዳሮች የመከበራቸው ሚስጥር በዋቄፈና እምነት ዋቀ ሁሉም ቦታ ስላለ ወንዞች፣ ሐይቆች፣ ተራሮች፣ የኦዳ ዛፎችና ጫካ የመሳሰሉት ሥፍራዎች የዋቃ መንፈስ ያለባቸው እንዲሁም የዋቀ ተዓምራት የሚታዩባቸው የተከበሩ ሥፍራዎች ናቸው ተብሎ እንደሚታመን ጥናቶቹ ያስረዳሉ፡፡

ኢሬቻ የሚከበርባቸው ተፈጥሮዓዊ ሥፍራዎች ክብር ያላቸው፣ ሰላማዊና የአምላክ መንፈስ ያለባቸው ናቸው ተብለው ስለሚታመኑ እንጂ በሥፍራው፣ በወንዙ፣ በሐይቁ፣ በኦዳው እንዲሁም በተራራው ማመን ማለት እንዳልሆነ አቶ ስንታየሁ ያብራራሉ፡፡

የኢሬቻ ምስጢራዊ ይዘቶች

ክረምት መውጣቱን ተከትሎ በበርካታ የኦሮሞ ሕዝብ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል የራሱ የሆኑ ምስጢራዊ ይዘቶች እንዳሉት ይነገራል፡፡ ይኼም ኢሬቻ የተፈጥሮ (የፍጥረታት ሕግና ሥርዓት) በዓል እንደሆነ ይገለጻል፡፡ በዋቄፈና እምነት ሁሉም ነገር በሕግና ሥርዓት ይተዳደራል የሚል እምነት አለ፡፡

በመሆኑም ምልካምና ቱሉ የራሳቸው ክብር፣ ሕግ እንዳላቸው ስለሚታመን ኢሬቻ የዋቀ ሥርዓት ሕግና ትዕዛዝ የሚሞላበት እንዲሁም ቀጣይነት እንዲኖረው የሚከበር በዓል ነው፡፡

በዕለተ ቀኑ ክብረ በዓሉ ሲከበር ልጃገረዶች ‹‹ማሬዎ ማሬዎ›› እያሉ የሚዘምሩት፣ ይኼም ማለት ሁሉም ነገር የተፈጥሮ ሥርዓትን ጠብቆ ዞሮ መምጣቱን ለመግለጽ እንደሆነ ጥናቶቹ ያስረዳሉ፡፡ በዚህ በዓል በፈጣሪና ፍጥረት መሀል ያለው ሥርዓት ሳይቋረጥ ሒደቱን ጠብቆ በመካሄዱ የሚከበር የምሥጋናና የምልጃ በዓል እንደሆነ ለማስረዳት ነው፡፡

ምልጃውና ምሥጋናው ክረምትና በጋ፣ ቀን ሌሊት፣ ብርሃንና ጨለማ፣ ልጅነትና እርጅና እንዲሁም ሕይወትና ሞት የማያቋርጡ ሒደቶች እንደሆኑ ለማሳየት ነው፡፡

ኢሬቻ ላይ ማን ይሳተፋል?

ኢሬቻ መከበር ከጀመረበት ጥንት ዘመን የኦሮሞ ሕዝብ በዓሉን መልካ ሞርሞር (ዓባይ)፣ ሀሮ ዋላቡ፣ ቱሉ ዋላል፣ ቱሉ ነሞዱሪ በሚባሉ ሥፍራዎች ሲያከብር እንደቆየ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

በመሀል አገርም ስድስቱ የዋቄ (አምላክ) ሐይቆች በሆራ ፊንፊኔ፣ ሆራ አርሰዴ ሆራ ኪሎሌ እንደሚከበር ይነገራል፡፡

ከዚህም ባሻገር ስምንቱ የዋቃ ተራራዎች በሚባሉት ጩቃለ ቱሉ፣ ኤረር፣ ቱሉ፣ ፍሪና ቱሉ፣ በስት በሚባሉ ሥፍራዎች ሲከበር እንደነበረ ይገለጻል፡፡ ከስድስቱ የዋቃ ሐይቆች የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ ቀዳሚ እንደነበር ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

የኢሬቻ በዓልን ኦሮሞዎች የተለያዩ ሃይማኖቶች ተከታዮች ማራቶሞ ክርስቲያን – ኦርቶዶክስ፣ ወንጌላውያን፣ ካቶሊክ፣ ሙስሊሞችና ዋቄፈታዎች በጋራ ያከብሩታል፡፡

ክብረ በዓሉ ሕዝቦችን በማስተሳሰር ረገድም ከፍተኛ ሚና እንዳለው ይታመናል፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ማክበር ጀምረዋል፡፡ በ2012 ዓ.ም. በተከበረው የሆራ አርሰዴ እና ሆራ ፊንፊኔ ከ30 በላይ ብሔረሰቦች በዓሉን ማክበራቸው ተነግሯል፡፡ ከዚህ ቀደም በበርካታ ሕዝቦች ሲከበር የነበረው በዓሉ ዘንድሮ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከ5000 ሰዎች በላይ መሳተፍ እንደማይችሉ ተገልጿል፡፡