ችግሮችን በመፍታት የገዳ ሥርዓት ሚና

ኦሮሞ የበለጸገ ባህል ካላቸው በኢትዮጵያ ከሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች መካከል አንዱ ነው። ብሔረሰቡ ካለው የህዝብ ቁጥር ፣ የመሬት ስፋት እና ተፈራራቂ የአየር ንብረት የተነሳ ባህሉንም ማበልጸግ ችሏል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ኦሮሞ በከፍተኛ ደረጃ የዳበረ ምሉዕ ሥርዓት እና የእያንዳንዱን ግለሰብ ህልውና ውስጥ በሁሉም መልኩ ዘልቆ የሚንጸባረቀው የገዳ ሥርዓት ነው። ይህ ሥርዓት የኦሮሞን ማህበረሰብ ህብረት እንዲኖረው የሚያደርግ ሲሆን በኢትዮጵያም ከሚገኙ አገር በቀል ዕውቀቶች ግንባር ቀደም የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው። ይህ ሥርዓት ምንም እንኳን አጀማመሩ በትክክል እንዲህ ነው ተብሎ ጊዜው ባይታወቅም የኦሮሞ ህዝብ በሥርዓቱ መጠቀም የጀመረው ከ500 ዓመት በፊት እንደሆነ የታወቀ እና የተመዘገ ነው። ዝነኛው የቦረና የኦሮሞ ታሪክ ሊቅ አሬሮ ራማታ በ1969 ዓ.ም 4 ሺ ዓመት ወደ ኋላ ተጉዞ የሥርዓቱን መነሻ አፈ -ታሪኮችን በማጣቀስ “ፕሮውቲ እና ሌሎች” ብሎ በ1981 በጻፈው መጽሐፍ አስቀምጧል።

የገዳ ሥርዓት የኦሮሞን እምነት፣ ፍልስፍናውን፣ ጥበቡን፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኑሮውን እንዲሁም የጊዜ አቆጣጠሩን ለአያሌ ዘመናት መርቷል። የእያንዳንዱ ማህበረሰብ አባል እንቅስቃሴ እና ሕይወት በገዳ ይመራል። ገዳ ሥርዓት የህብረተሰቡ ህግም ነው፤ ኦሮሞ ራሱን የሚያስተዳድርበት ኢኮኖሚውን የሚያሳድግበት እና የሚንከባከብበት የኑሮውንም ልዕልና ከዳር ያደርስልኛል ብሎ የሚቀይሰው በገዳ ሥርዓት ነው። እኛም ይህ የበለጸገ አገራዊ እውቀትን እንዴት ለሚገጥሙን ችግሮች መፍቻ ማድረግ እንደምንችል እና በአጠቃላይ የገዳ ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ ሂደቱ ምን ይመስላል የሚለውን ሃሳብ በማንሳት ከቀድሞ አባገዳ በየነ ሰንበቶ ጋር ቆይታ አድርገናናል መልካም ንባብ።

የገዳ ሥርዓት የዴሞክራሲ እና እኩልነት ፖለቲካ ሥርዓት መሰረት ሆኖ የሚያገለግል ነው የሚሉት አባገዳ በየነ ሰንበቶ በዚህ ሥርዓት የህዝቡን ጉዳዮች የማስተዳደር እና ሕግ የማውጣት ሰስልጣን የህዝቡ እንደሆነ ይናገራሉ። እንደ አባገዳ በየነ ገለጻ ማንኛውም ወንድ የሆነ እና የገዳ ደረጃ ያለው የመመረጥ እና የመምረጥ ሙሉ መብት አለው፤ ምንኛውም ሰው ያለአንዳንች ይሉኝታ ወይም ፍርሃት አስተያየቱን በየትኛውም አደባባይ ለማሰማት መብት አለው። የገዳ ሥርዓት የወንዶችን የዕድሜ መደብን መሰረት አድርጎ የኦሮሞ የሕዝብ በመንግስት ሕዝብ ወይም ዴሞክራሲ ወግ የሚተዳደርበት ሥርዓት መሆኑ እሙን ነው፤ ገዳ አንድ ዓይነት ተቋማዊ ስራ ብቻ የሚከናወንበት ሳይሆን ፈርጀ ብዙ እና አያሌ ዘርፎች በውስጡ ያካተተ፤ የኦሮሞን ሁለተናዊ ህይወት በሁሉም አቅጣጫ የሚመራ ሥርዓት እንደሆነም ጠቅሷል።

በሥርዓቱም ውስጥ የሚከተሉት ተቋማት ይገኛሉ፤ ጉዲፈቻ ወይም ልጅ የመውሰድ ሥርዓት፣ ጉማ ወይም የእርቅ ሥርዓት፣ ሞጋሳ ወይም በራስ ፍላጎት ኦሮሞነትን የመቀበል ሥርዓት፣ ቦኩ ወይም የሕግ ሥርዓት፣ ከለቻ ወይም በወንዶች የሚያዝ የቃለ መሃላ መጠበቂያ የክብር ዕቃ እና የማስፈጸሚያ ሥርዓት ፣ጫጩ ወይም በሴቶች የሚያዝ ፣ቃሉ ግጭትን የመፍቻ ሥርዓት … እና የመሳሰሉ ተቋሞች አሉ። አባገዳ በየነ ይናገራሉ የእያንዳንዱ የገዳ ሥልጣን ዘመን 8 ዓመት ነው።

በገዳ ሥርዓት የሥልጣን እርከን እና የስራ ክፍፍል

የገዳ ሥርዓት አስራ አንድ ደረጃዎች ሲኖሩት ደረጃዎቹም በዕድሜ የተወሰኑ ናቸው። ታዲያ እያንዳንዱ ደረጃ እና እርከን የራሱ የሆነ ግላዊ እና ማህበረሰባዊ ኃላፊነት እንዳለበት የቀድሞ አባገዳ በየነ ሰንበቶ ይናገራሉ። እንደ አባገዳ በየነ ሰንበቶ ገለጻ የገዳ ሥርዓት መነሻ ዳበሌ ሲሆን ዕድሜያቸው ከአንድ ዓመት እስከ ስምንት ዓመት ሲሆን እንደነ ፎሌ፣ ቁንዳላ፣ ኩሳ ፣ራባ ዶሪ፣ ገዳ፣ ዩባ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ፣ ጋዳሞጂ፣ በስተመጨሻም ጃርሳ የሚባለው ደረጃ ማለትም ከ80 ዓመት በላይ ያላቸውን አዛውንቶች የሚያጠቃልል ነው።

አባገዳ በየነ ሰንበቶ ይናገራሉ አንድ የብሔረሰቡ ተወላጅ የሆነ ሰው ከአንዱ ደረጃ ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ እያለ እየተሸጋገረ ሲሄድ በህብረተሰቡ መካከል ያለው የስራ ድርሻውና አኗኗሩም እንዲሁ ይለዋወጣል። አባ ገዳ በየነ

 ነገሩንም በምሳሌ ሲያስረዱ በቁንዳላ በኩምሳ በራባ ዶሪ የሽግግር ወቅቶች ማለትም ለ24 ዓመታት በእነዚህ ደረጃዎች ውስጥ የሚያልፉት ሁሉ ስለ ጦርነት ጥበብ፣ ስለ ኦሮሞ ታሪክ፣ ፖለቲካ፣ ክብረ በዓላት፣ ህግጋት እና አስተዳደር ወዘተ ይማራሉ። ከዚህ በኋላ በ40 ዓመት ዕድሜ አካባቢ ወደ ገዳ ወይም ሉባ መደብ ሲገቡ ህብረተሰቡም ለማስተዳደር የሚያስችል ስለመንፈሳዊ ሆነ ክብረበዓላት አከባበር ምንኛውም እውቀት ያካብታል ብለዋል።

የስራ ክፍፍሉንም የቀድሞ አባገዳ በየነ ሲያስረዱ በሥርዓቱ በዘጠኝ የሥራ ክፍፍል ሲኖር አባ ቦኩ ፕሬዚዳንት ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን ሁለት ምክትሎች ደግሞ ይኖሩታል ሌላኛው ደግሞ አባ ጨፌ የሚባሉት ሲሆኑ እነዚህ ደግሞ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ በመሆን ያገለግላሉ፤ አባ ገዳ በየነ ይናራሉ አባ ዱቢ፣ አባ ሴራ ፣ አባ አለንጋ የምክር ቤት እና የሕግ ባለሙያ ሆነው ያገለግላሉ አባዱላ እና አባ ሰኣ ደግሞ የጦር አበጋዝ እና የግምጃ ቤቱ ተጠሪ ሆነው ያገለግላሉ።

ገዢው የገዳ መደብ በጥቅሉ በገዳ ጨፌ እጅግ ከፍተኛውን ስልጣን የተቀዳጀ እና ውሳኔውም የመጨረሻ እንደሆነ የሚናገሩት አባገዳ በየነ ይህ ሸንጎ አጠቃላዩ የህዝብ ተወካዮች አስቀድሞ በተቆረጠና በተወሰነ ሰዓት ተገኝተው በወቅቱ በስልጣን ላይ ያሉትን ባለስልጣናት የሚፈልግባቸውን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ስለመወጣታቸው ግምገማ የሚካሄድበት ሸንጎ ነው። በዚህ ጉባዬ ላይ በሃላፊነት ላይ ያሉት ባለስልጣን የሚፈለግባቸውን አደራ በአግባቡ ካልተወጡ ከሥልጣናቸው ይሻሩና በሌላ ቡድን ማለትም ተመሳሳይ የገዳ መደብ ወይም “ሉባ” ከሆኑት መካከል ተመርጠው እንዲተኳቸው እንዲደረግም አባገዳ በየነ ይናገራሉ።

የግጭት አፈታት

ከእያንዳንዱ የኦሮሞ ጎሳ ሉባ ሆኖ የተመረጠው ሰው ወደ ጨፌ ገዳ ሸንጎ ከደረሰ በኋላ አባ ጨፌ ለሚባለው ጊዜያዊ የሸንጎ አስተባባሪ ያመለክታል፤በዚህም መሰረት ይህ ሰው ህጋዊ የአባ ቦኩ ቦታው የሚሰጠው እንደሚሆን የሚናገሩት የቀድሞ አባ ገዳ በየነ አንድ በግልም ይሁን በቡድን ጉዳት የደረሰበት ግለሰብ የደረሰበትን ችግር በማስረዳት ለዚሁ ምክር ቤት አቤት! ይላል።

ታዲያ ይህ ክስ አባቶቹ ጋር ከደረሰ በኋላ በጨፌ አባቶቹ ከተሰበሰቡ በኋላ በቀረበው ክስ ላይ ይወያያሉ፤ በኋላም በዳይንም ተበዳይንም በመጥራት አባቶች የተለያዩ ጥያቄዎች ይጠይቋቸውና በጉዳዩ መክረው መልስ እነደሚሰጧቸው የጊዜ ቀጠሮ ሰጥተው የእለቱ ውሎአቸውን ይፈጽማሉ፤ በቀጠሮው ቀንም ሲገናኙ አባቶቹ ሁለታችሁም

 ጉዳያችሁን ለኛ ሰጥታችኋል ወይ ብለው እንደሚጠይቁ የሚናገሩት አባገዳ በየነ ሁለቱም ባለ ጉዳዮች አዎ! ብለው ከመለሱ በኋላ በከቀረበላቸው ክስ ላይ የደረሰበትን የውሳኔ ሃሳብ ያቀርባሉ፤ በዳይ ተበዳይን የገዳ አባቶች በሚያዙት መሰረት ይቅርታ ከመጠየቅ ጀምሮ ካሳ እስከመስጠት የፍርድ ውሳኔ ይበየንበታል እርሱንም የመፈጸም ግዴታ አለበት ፤ ታዲያ በገዳ አባቶች ከተወሰነው ውሳኔ በዳይም ይሁን ተበዳይ ወደ ኋላ እንዳይሉ መሃላ በማስፈጸም ለዚህም ምልክት እንዲሆንም በአባቶቹ ፊት ከብት ታርዶ እርሱንም በመሻገር የእርቁ ሥርዓት ይከናወናል።

አባ ጋዳ በየነ አሁንም ይናገራሉ ከዚህ በኋላ ወደ ኋላ መመለስ ፣አሻፈረኝ ማለት ፈጽሞ አይታሰብም ፤ ነገር ግን ይህንን ሁሉ የእርቅ ሥርዓት አልፎ በውሳኔው ሳይስማማ ለይስሙላ አባቶቹን እሺ ብሎ የውሳኔውን ሃሳብ የማይተገብር ከሆነ ግለሰቡ አባቶቹን ብቻ ሳይሆን የኦሮሞ ብሔረሰብን በሙሉ እንደናቀ እና እንደከዳ ይቆጠራል፤ ከማህብረሰቡም ይገለላል፤ ኀዘን ቢደርስበት የሚያጽናናው አይኖርም፤ እራሱ ቢሞት የሚቀብረው የለም፤ ብቻ በቁሙ እንደሞተ ይቆጠራል። ስለሆነም የአባቶችን እርቅና ምክር የማይተገብር አይኖርም ከጥቂቶች በስተቀር የሚሉት አባገዳ በየነ የእነዚህም ሰዎች ኑሮም እጅግ ከባድ እንደሚሆንባቸውም ገልጸዋል።

የቀድሞ አባገዳ በየነ ይህ ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ሥርዓትን በዚህም ዘመን ከእነ ሙሉ ክብሩ መኖሩን ጠቅሰው አሁንም እንደ ቀድሞ የገዳ ሥርዓትን ብሔረሰቡም በአጠቃላይ መላው አትዮጵያ ለመመካከሪያነት ፣ ለግጭቶች ማስወገጃነት ፣ለእርቅ ሥርዓት እንዲሁም ለተለያዩ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች ብንጠቀምባቸው አሁን እየደረሱ ያሉ ችግሮችን በቀላሉ መቆጣጠር እና ማስቆም ይቻላል።

ከእዚህ ቀደም መንግስት እንዲህ ባሉ ባህላዊ ሥርዓቶች ውስጥ እጁን አስገብቶ ስለነበር ማህበረሰቡም በሥርዓቶቹ እምነት አጥቶ ነበር አሁን ይመለከተኛል የሚል ማንኛውም አካል የተበላሸውን በማረም፤ የጎደለውንም በመሙላት የገዳ ሥርዓትን ወደ ቀድሞ ክብሩ እና ስልጣኑ በመመለስ እንደሚኖርበት ቀድሞ አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ ያሳስባሉ።

መልዕክት እና ስንብት

የገዳ ሥርዓት አገር በቀል የሆነ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመሆኑ እንደ አገር ሆነ እንደ ኦሮሞም እንደቀድሞው ጥቅም ላይ በማዋል በማህበራዊ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓቶች ላይ አስገራሚ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል የሚናገሩት የቀድሞ አባገዳ በየነ ሰንበቶ ደምን ለማድረቅ፣ እርቅ እና ሰላምን ለማምጣት…ለዘርፈ ብዙ ትርፎች በዚህ ዘመን ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።

አያሌ የማህበረሰብ ተመራማሪዎች በተለያዩ ጊዜአት ስለገዳ ሥርዓት ጥናት አድርገዋል ብዙዎቻቸውም ይህ ሥርዓት በልዩ መልኩ ዴሞክራቲክ ስለመሆኑ መስክረዋል። ከእነዚህም መካከል በሥርዓቱ ጥልቅ ጥናት ያደረጉት ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ እንዲህ ብለዋል “…የሰው ልጅ በዘገምተኛ ሂደቱ ከተቀዳጃቸው እጅግ አስገራሚ እና ገምቢ ከሆኑት የሽግግር ዕድገቶች ውስጥ ገዳ አንዱ ነው፤ በእርግጥም ደግሞ እጅግ አስደናቂ ከሆኑት የአፍሪካ ማህበራዊ ፖለቲካዊ መዋቅሮች ውስጥ አንዱ እና በሌላው አካባቢ ህዝብ ኑሮ ላይ ተጽህኖ ያሳደረ ሥርዓት ነው ፤ በመሆኑም በርካታ አጎራባች ህዝቦች እንኳ ገዳ መሰል ልምምድ እንዳላቸው ታውቋል። ” ይህ ሃሳብ የአባ ገዳን ሰንበቶን በእጅጉ የሚደግፍ እና የሥርዓቱንም ጥልቅ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታንም የሚሳይ ነው።

አባ ገዳ በየነ አሁንም ይናገራሉ የትኛውም ጉዳይ እንዲሁም ግለሰብ ከአገር ሰላም አይበልጥም ፤ስለሆነም ጊዜ እየጠበቁ በአገር እና በህዝብ ላይ የሚደረጉ ህገወጥ ድርጊቶች እንደ ገዳ ሥርዓት ባሉ አገራዊ በቀል በሆኑ እውቀቶች ሥርዓቶች መልክ ሊይዙ ይገባል።

እኛም ልክ እንደ ኦሮሞ ብሔረሰብ የሌሎችም ብሔረ ብሔረሰቦች የበለጸጉ አገራዊ እውቀቶችን በማምጣት እና ለአገር ጥቅም እንዲውል በማድረግ የበለጸገች ሰላሟ የበዛ አገር መገንባት ይቻላል፤ መልዕክታችን ነው። ኢትዮጵያ የመቻቻል የሰላም እና የብልጽግና ምድርነቷ ይቀጥላል። ሰላም!

አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2012

 አብርሃም ተወልደ