“ሶንጎ” የዳኝነት ስርዓት በሲዳማ

በጽጌረዳ ጫንያለው

በአገራችን በርካታ ባህላዊ እሴቶች አሉ። የእርቅ፣ የሰርግ፣ የሃይማኖታዊና ባህላዊ እንግዳ መቀበያ፣ የሀዘን… ብቻ እንደየ ብሄረሰቦቹ እና አካባቢያቸው ችግሮቻቸውን የሚፈቱበት፣ ደስታቸውን የሚካፈሉበትና ሀዘናቸውን የሚተዛዘኑበት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊም እሴቶች አሉ። ለዛሬው የምናየው ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ከሆኑት መካከል የሲዳማ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴን ይሆናል። የሲዳማ ዞኑ ባህል መምሪያ የላከልንን መረጃ እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል።

የሲዳማ ብሔር በታሪክ ለረጅም ዘመናት ማዕከላዊ መንግሥት ሳይመሰርት በሉዋ ሥርአትና በጎሳዎቹ ራስ ገዝ የአስተዳደር መዋቅሮችን ሲከተል የቆየ ነበር። ከጥንት ጀምሮ ሲመራባቸውና ሲተዳደርባቸው የኖሩት ባህላዊ ተቋማት፣ እሴቶች፣ ልማዳዊ አሠራሮችና የእምነት ሥርዓቶችም አሉት። ከእነዚህ መካከል የአስተዳደርና የዳኝነት፣ የግጭት አፈታት ባህላዊ ሕጉ አንዱ ነው።

በሰው ልጅ ማህበራዊ ሕይወት ውስጥ ግጭት አይቀሬ ነውና ሰዎች ግላዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ሲሉ የሌሎችን ሰዎች ፍላጎት ሊነኩ ይችላሉ። በዚህም ግጭቱን ለማብረድ የተለያዩ ባህላዊ መፍትሄዎች ተግባራዊ ያደርጋሉ። እናም ሲዳማዎች ችግራቸው መፍትሄ እንዲያገኝ ለማድረግ ሶንጎን ማዕከል አድርገው ይዳኛሉ። የሶንጎውን ደረጃ አውጥተው ችግሮች ተከፋፍለው እንዲዳኙ ያደርጋሉ። ይህም በየደረጃው የተከፋፈለ ሲሆን ኦሉ ሶንጐ፣ አይዱ ሶንጐ፣ ቦሶቴ ሶንጐ፣ ጋሬቴ( ሞቴ) ሶንጐ ይባላሉ።

ኦሉ ሶንጎ

ይህ የሶንጎ ደረጃ የሲዳማ ህብረተሰብ አሠፋፈር የጎሳና የዘር ሀረግ ዘውግን የተከተለ ነው። የሚቀርበው ጉዳይ የቤተሰብና የቤተዘመድ ቅራኔ ሲሆን፤ ዳኞቹም የቤተሰብ ሽማግልዎች ናቸው። ጉዳዮቹ በባህሪያቸው በጣም ያልተካረሩና አንተም ተው አንቺም ተይ በመባባል ሊቀሩ ይችላሉ። ሆኖም ተበደልኩ ባይ አልፌ ሄጄ ትክክለኛ ፍትህ አገኛለሁ ብሎ ከተነሳ በሩ ዝግ አይሆንበትም። ነገር ግን ባለጉዳዩ ዞሮ ዞሮ ከቤተሰብ የሚወጣ አይሆንምና የነገን በማሰብ አልፎ ሲሄድ አይታይም።

አይዱ ሶንጎ

ይህ ደረጃ ደግሞ ከመጀመሪያው ከፍ ያለ ሲሆን፤ በአብዛኛው የሚያያቸው በኦሉ ሶንጎ እልባት ያላገኙ ጉዳዮችን ነው። ለእርሱም በቀጥታ የሚቀርቡ ጉዳዮች ይኖሩበታል። ለምሳሌ በሁለት መንደሮች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች የሚቀርቡት ለአይዱ ሶንጎ ነው። የዚህ ደረጃ አባላት ከየአካባቢዎቹ የተወጣጡ ግለሰቦችና ከአንድ ሌላ ገለልተኛ ቀበሌ የመጡ ታዛቢዎች ሊሆኑ ይችላሉ።

ቦሶቴ ሶንጎ

ለዚህ ደረጃ አባላት የሚሆኑት የሚመረጡት ከአይዱ ሶንጎ የተወጣጡ መሪ ሽማግሌዎች (ጭሜሳዎች) ናቸው። የመንደሩ ነዋሪም በሶንጎ ላይ በሰፊው ይሳተፍበታል። ሶንጎው የራሱ የሆነ የመሰብሰቢያ ቦታ ወይም ጉዱማሌ ያለው ሲሆን፤ በታችኛዎቹ ሶንጎዎች ሊፈቱ ያልቻሉ፣ ከእነርሱ አቅም በላይ የሆኑና ከፍተኛ ውሳኔ የሚሹ ከባድ ጉዳዮችን የሚያይ ነው።

የሞቴ ሶንጎ

ይህ ሶንጎ በተለያዩ መጠሪያ ስሞች የሚታወቅ ሲሆን፤ አንዳንዶች የቤተዘመድ ስብስብ ሶንጎ መሆኑን ለመግለጽ የ‹‹ጋሬ›› ‹‹የጋሬቴ” ይሉታል። ሌሎች ደግሞ ሶንጎው በሞቴው መመራቱን ለመንገር የሞቴ ሶንጎ እያሉ ይጠሩታል። በሶንጎው ሞቴው በህዝብ ተመርጦ ስልጣን የሚያገኝ ሳይሆን በዘር ሀረግ ነው። ለዚህ ደግሞ ስልጣኑን የሚረከበው ልጅ በምሥጢር በተለያየ መንገድ ተፈትኖ እንዲያልፍ ይደረጋል። ልጁ በሥራ ቅልጥፍና፣ በአነጋገርና በብስለቱም ይገመገማል።

በሶንጎው ሌሎች አባላት የየአካባቢያቸው የኦሉ ሶንጎ መሪዎች ሲሆኑ፤ የሚያገለግሉት በየስልጣን እርከናቸው በመወከል ነው። ሌላ ከየቤተዘመዱ ጉባኤ የሚሰበሰቡ ማገልዎችን ይጨመሩበታል። የዚህ ሶንጎ አባላት የሥነ ምግባር ችግር ካልገጠማቸው በስተቀር የአገልግሎት ዘመናቸው የዕድሜ ልክ ነው። የሥራ ድርሻቸውም ከበታችኞቹ በአቤቱታ መልክ የሚመጡትና ሌሎች ወንጀል ነክ ጉዳዮች ናቸው። ስለዚህ እነዚህን ጉዳዮች መርምረው ተገቢውን ውሳኔ ይሰጣሉ። የእምነት ሥርዓቱን የማስፈጸም ሥራንም ይሰራሉ። ይህ ሶንጎ ቋሚ የመሰበሰቢያ ቀናትና ቦታ ያለው ሲሆን፤ በህብረተሰቡ ዘንድ የመጨረሻው የፍትህ ሶንጎ ነው።

ባህላዊ የአስተዳደርና የዳኝነት ተቋማት በመሠረታዊ ጉዳዮች፣ በአወቃቀርና በግጭት አፈታት ዘዴዎቻቸው ከሞላ ጎደል ተመሳሳይነት አላቸው። ሆኖም በስያሜና በቅደም ተከተል ደረጃ ግን በየጐሳዎቹ መጠነኛ ልዩነቶች ይታይባቸዋል የሚለው መረጃው፤ የሶንጎ የእርከን ደረጃው ከቤተሰብና ቤተዘመድ ሶንጎ (ሸንጐ) ጀምሮ እስከ ሞቴ ሶንጎ (ጐሳ ሸንጐ) ድረስ እየሰፋና ተከታታይነቱን ጠብቆ የሚሰራ መሆኑን ያስቀምጣል።

የዳኝነት ሥርዓት ክዋኔዎች

በሲዳማ ዳኝነት ስርዓት ወቅት ቀድመው የተገኙት የሶንጉው ታዳሚዎችና ጪሜሳዎች (ሽማግሌዎች) ቢኖሩም መገኘት ያለባቸው አካላት ካልመጡ ጉዳይ አይታይም። ሆኖም በደንብ እስኪሰባሰቡ ብሄሩን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ውይይት ይደረጋል። የዳኝነት ሂደቱ የሚመራው ጪሜሳ በሚባሉት ነውና ጉዳዩ እንዲጀመር የሚያደርጉትም እነርሱ ናቸው።

ባህላዊ የግጭት አፈታት ሂደቱ ከ‹‹ቃጣሮ›› ክስ ከማቅረብ ይጀምራል። ተበደልኩ፣ ተጎዳሁ፣ የሚለው ሰው በአካባቢው ላሉ ጪሜሳዎች ወይም ለሶንጎ መሪዎች ጉዳዩን ያሳውቃል። ከዚያ ጉዳዮቹ የሶንጐ ደረጃዎችን ጠብቀው በይግባኝ መልኩ ወደ ላይ የሚሄዱ ይሆናል። ነገር ግን ክሱ የሚቀርብበት ደረጃ እንደየ ጉዳዩ ክብደትና እንደ ከሳሹ ፍላጎት ይወሰናል። በባህሉ ዘንድ ተከሳሽን እንዲቀርብ ማድረግ ‹‹ሶካ›› የሚባል ሲሆን፤ በብዙዎቹ ጎሳዎች ተከሳሹ የሚጠራው በቃል ነው። አሁን ግን ተቀይሮ በጽሁፍ መጥሪያ ወረቀት ሆኗል። ስለዚህ ይህ ከተደረገ በኋላ የፍትህ ሥርዓቱ ከ “ጋልቲኖ” ይጀምራል። ጋልቲኖ ማለት በሥፍራው ቀድመው ለተገኙት የሶንጐ አባላት ሰላምታ ማቅረብ ነው። እናም በባህሉ መሰረት ከሰዓት በኋላም ቢሆን ‹‹ሶንጐ ጋልቲኒ›› ማለትም እንደምን ዋላችሁ ይባባላሉ።

ሰላምታው ከቀረበ በኋላ ደግሞ “ባዲሪ ማይኖ” በማለት ስለሀገር ምን አዲስ ነገር አለ? ይባላል። ምክንያቱም የባህል የመረጃ ልውውጥ ከፍተኛ ዋጋ ይሰጠዋልና። ይህ እንዳለቀም ‹‹ማማጋሺኑሞ?›› ወይም የት ነበር ያሳደርነው? በማለት ይጠያየቃሉ። መልስ ካገኙም በኋላ ባለፈው የሶንጐ ዕለት ተጀምሮ ያልተጠናቀቀ ጉዳይ ካለ ቅድሚያ በመስጠት ይጀምራሉ። አንዳንድ ጊዜ ግን በአጣዳፊ መፈታት ያለበት ከባድ ችግር ከመጣ ለእሱ ቅድሚያ ሰጥተው ውሳኔ ያስተላልፋሉ።

በሲዳማ ባህል አዲስ ጉዳይ መቀበልና ማዳመጥ “አፋቶ ማጪሻ” ይባላል። ባለጉዳዩ ጉዳዩን ሲያቀርብ ደግሞ “ኤያ!” (እህ!) በማለት የሚቀበለው በዚያ ሶንጐ ላይ ካሉት ጪሜሳዎች አንጋፋው ነው። ከዚያ ከሳሽ “ክስህን አሰማ” ይባልና በደሉን ያስደምጣል። ተከሳሽም “ማያቶ” ወይም ‹‹ዲአፊቶ”? አንተስ ምን ትላለህ?” ተብሎ ይጠየቃል። ተከሳሹም ከሳሹን መበደል አለመበደሉን ይናገራል። ተከሳሹ የቀረበበትን ክስ አምኖ ይቅርታ ከጠየቀ ጉዳዩ በአጭሩ ይቋጫል። ካልሆነ ግን የሶንጐው አባላት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ከታዳሚው ሀሣብና አስተያየት ወደመቀበሉ ይገባሉ።

የታዳሚውን ሀሳብ በመቀበልና በማስተናገድ በህዝቡ በስፋት የሚታወቀው የ “አፊኒ” ደንብ የሚባለው ሲሆን፤ ሀሳብን የማንሸራሸር ሂደት በአግባቡ እንዲከናወን የሚያደርግ ነው። ሆኖም ይህንን የሚተላለፍ ነውረኛ ቃሎችን የሚናገር ከተፈጠረ እቀባ እንዲጣልባቸው ለሶንጐው ሰብሳቢና ጭሜሳዎች ይተዋል። ኃላፊነቱ የተሰጣቸው አካላትም ‹‹ኢቲሱሞሄ›› በማለት ንግግራቸውን ያስቆማሉ። በሂደቱም ተናጋሪው ከእቀባ አድራጊው ሽማግሌ ጋር በዕድሜ እኩል ከሆነ ‹‹ሐኮ ዮሮሞሄና›› ማለትም እዚህ ላይ ላስተካክልህ ሲል በዕድሜና በደረጃ የሚበልጠው ከሆነ ደግሞ ‹‹ሶቃሚሞሄና›› ወይም ከዚህ ጋር ልላላክህ በማለት ያርማል።

የእውነት ዋጋ

በሲዳማ ባህላዊ ዳኝነት ‹‹ሃላሌ›› ወይም ሀቅ እጅግ ከፍ ያለ ቦታ አለው። ከሰዎች ፍላጐት፣ አመለካከት፣ ሥነ-ምግባር፣ ስምምነት ውጪ ያለ ተፈጥሯዊ እውነታ ምንም አይተገበርም። ስለዚህ በሀሰት መከራከር አይፈቀድም። በባህሉ “አዳ” ተባለ ማለት ተቀባይነት ያለው፣ መሆን ያለበት፣ ሊሆን የሚገባው፣ ህብረተሰቡ የተቀበለው ሥነ-ምግባር ነው። እናም ህብረተሰቡ የተቀበላቸው የሥነምግባር ደንቦች ሲጣሱ ደግሞ እውነት ተጣሰ ነውና ይህ አይፈቀድም። በዚህም ዳኝነቱ እውነትን ማሳያ ነው። ሌላው እውነት ሲፈለግ “ሀዮ” የሚሉት ሲሆን፤ እውነትን ለማግኘት በምክንያት ጐንግኖ የሚያውጣጡበት ስርዓት ነው።

እርቅና መልኩ

በሲዳማዎች ባህል ዘንድ እርቅ የሚፈጸመውም እውነቱ ተገልጦ ከወጣ በኋላ ነው። እንደ ጉዳዩ ክብደት የተለያዩ “ጉሙሎ” ወይም የቅጣት ውሳኔዎችን ይደረጉና እርቅ ይወርዳል። በተቃራኒው የተገኘው መረጃ ግን ውሳኔ ለመስጠት በቂ ካልሆነ ጉዳዮችን የማጣራትና መረጃ የመሰብሰብ ሂደቱ ወይም ‹‹ቆራ›› እንዲከናወን ይደረጋል። ሆኖም በሲዳማ ጐሳዎች የአምልኮ ቦታዎች ላይ ቆሞ ውሸት መናገርና መካድ በቤተሰቡ ላይ ሞትን፣ በትውልዱ ላይ ርግማንን፣ ህመምን፣ መጥፎ አጋጣሚን ይፈጥራል ተብሎ ስለሚታመን ይህንን የሚያደርግ አይኖርምና እርቅ በፍጥነት ይፈጸማል። እርቁም የተለያየ መልክ አለው።

ፊጫ

በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠውና አፈታቱም ውስብስብ የሆነ የደም እርቅ ነው። በባህሉ ነፍስ መግደል የተከለከለ ቢሆንም በተለያዩ አጋጣሚዎች ነፍስ ሊጠፋ ይችላል። በዚህም ነፍስ በእጁ የጠፋበት ሰው ቤተዘመድ ለሞቴው አለዚያም ለበታች የሶንጐ መሪዎች ይነግሩና በእርቅ እንዲፈታ መንገድ ይፈልጋሉ። ገዳዩ ከሟች ወገኖች ሊሰነዘርበት ከሚችለው ጥቃት ራሱን ለማዳን የእርቅ ሂደቱ እስኪጀመር ድረስም በሞቴው ቤት ተጠልሎ እንዲቆይ ያደርጋሉ።

ይህ የእርቅ ሥርዓት በተለያዩ ጐሳዎች ዘንድ መጠነኛ ልዩነቶች ይታይበታል የሚለው መረጃው፤ የሟች ቤተሰብና ወገን ለመበቀል ሟችን ሳይቀብሩ ለተወሰኑ ቀናት ይቆያሉ። በዚህም የገዳይ ወገኖች ለአስከሬኑ ከፈን እንስጥ በማለት ሽማግሎችን እንዲጠይቁ ይሆናል። ነገር ግን ሽማግሌዎች ነገሩ እንዳይባባስ በማሰብ ገና ነው ብለው ጥፋት እንዳይከተል ጎን ለጎን የእርቅ ሂደቱን ለማፋጠን የሚያስችሉ ሥራዎችን ያከናውናሉ። የሟች ወገኖችንም አስከሬኑን እንዲቀብሩ ይገፋፋሉ። እርቅ እስኪደረግ ድረስ የሟችና የገዳይ ወገኖች በምንም ዓይነት አጋጣሚ እንዳይገናኙም ያደርጋሉ። ይህ ሥርዓት ደግሞ በብሔሩ አጠራር “ቄጌ” ይባላል።

በመጨረሻ በተቆረጠው ቀን በዳኝነት ሥፍራው ሁለቱ ወገኖች እንዲገኙ ይደረጋል። ሞቴውና ረዳቶቹም የሲዳማን ታሪክ፣ አባባል፣ ወግና ልማዶችን ምሳሌዎችን እየጠቃቀሱ ካሁን በኋላ ከልባቸው ይቅር ተባብሉ ይሏቸዋል። ወንድማማች ሆነው እንዲኖሩም ይመክሯቸዋል። ከዚያ ለፊጫ ስርዓት የሚሆን የእንስሳት ዕርድ ይፈጸምና እርቅ ይወርዳል። ይህም ‹‹ችፊ›› ይባላል። ከብቱ ታርዶ ደሙ ይቀዳና ሁሉም ሰው ግንባሩን ይቀባል፤ የከብቱ የጐድን አጥንትም ይሰበራል። ይህ ማለት በመካከል ቂም የለም የሚለውን ምሳሌ ይይዛል።

የካሳ ክፍያ አይነቶች

በሲዳማ ‹‹ዳኖ›› ወይም በስህተት የተፈጸመ ግድያና ሆን ተብሎ የተፈጸመ ግድያ ካሳቸው እኩል አይደለም። ሆን ብሎ ያደረገው የደም ካሣን ወይም በባህሉ “ጉማ”ን ይጠየቃል። ስለዚህም ገዳይ ብቻውን ስለማይችለው ጐሳውን ጭምር ያስቸግርና ይከፈላል። ሆኖም ግድያው የተፈጸመው በድንገት መሆኑ ከተረጋገጠ ግን የገዳይ እናት ለሟች እናት ብሉኮ “ሴማ” ትገዛለች። ለቤተሰቡ የሀዘን ማስረሻ ይሆን ዘንድ ደግሞ ለእህቱ ጊደር፣ ለአባቱ ገንዘብ እንዲሰጣቸው ይደረጋል። እርቅ ወርዶ የሟች ወገኖችን ለማጽናናትና እንዲህ ዓይነት ችግር በህብረተሰቡ ላይ እንዳይደርስ ለ”ማጋኖ” ወይም ፈጣሪ-አምላክ ምስጋና ይቀርብና “ማላዎ” ወይም ጠጅ ቀርቦ የሟችና የገዳይ ወገኖችና የሶንጐው አባላት በአንድ ላይ ይጠጣሉ።

ግጭቶች ሲከሰቱ በሰዎች ላይ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳቶች ይደርሳሉ። ለዚህም በዳይ በዓይነት ወይም በገንዘብ ካሣ ይከፍላል። ሌላው በሲዳማ ባህል ዘንድ የሚከፈል ካሳ “ሀራፎ” የሚባለው ነው። የአካል ጉዳት የደረሰበት፣ ደሙ የፈሰሰበት ሰው የሚያገኘው ካሳ ነው። ስለዚህ ይህ ካሳ በግ ወይም ፍየል ይሆናል። ሲዳማዎች “ፈላ” እየተባለ የሚጠራም የካሳ ክፍያ አይነት አላቸው። ካሳው ከበድ ሲሆን፤ የቅቤ፣ የገብስ፣ የከብት፣ እና የመሳሰሉት ሊጠየቁ የሚችሉበት ነው። “ጭንጮ” የሚባለው ደግሞ የሟች ቤተሰብን ለማጽናናት የሚከፈል ካሣ ነው። በአጠቃላይ ይህ ባህላዊ ሥርዓት ለተጎዳ ችግር ማስረሻ፣ መፍትሄ መስጫና ከማህበረሰቡ ጋር በቀጣይነት በፍቅር መኖሪያ በመሆኑ ልንጠቀምበት ይገባል እያልን ለዛሬ ሀሳባችንን ቋጨን። ሰላም!

አዲስ ዘመን ኅዳር 7/2012